28/12/2018
አይነጋ መስሏት
‹‹ምነው ስትጮህ አልሰማንህምሳ!››
--- ---- -----
ሰው የፈለገውን ፓርቲ የመደገፍ መብት አለው፡፡
‹‹እሰይ ተስማምቶኝ ደግፌው ነበር›› ማለት እና አቋም ይዞ መከራከርም የሚያስከብር ምግባር ነው፡፡ የምወደው ድምጻዊ ንዋይ ደበበ ሃሳቡን ቀይሮ ከ‹‹ቀድሞው መንግስት›› ጋር ሲያብር አልተቀየምኩትም፤ምክንያቱም መብቱ ነው፡፡ ሰለሞን ተካልኝ ስለ አቶ መለስ ቅንድብ ሲዘፈን ራሴን በግርምት ከመነቅነቅ በቀር በአደባባይ አልወቀስኩትም፣ ምክንያቱም መብቱ ነው፡፡ ትእግስት ወይሶ በአቶ መለስ ለቅሶ ላይ ከጊዜ ማጣት የተነሳ ቀበቶ እንኳን ስላለመታጠቃቸው እያወራች ስታነባ ከመሳቅ በቀር እንዴት እንዲህ አለች ብዬ አልተናገርኩም፣ ይሄም መብቷ ነውና፡፡
ሰራዊት ፍቅሬና ሰራዊቱ ዘመን ካገነናቸው ተጠግተው ሲበለፅጉም በግሌ ከማጉረምረም ውጪ ለምን ይሄን ፓርቲ ደገፉ ብዬ ቡራከረዩ አላልኩም፣ የተመቻቸውን መደገፍ መብታቸው ነውና፡፡
ነገር ግን እንደ ሠራዊት ያለ ሰው እንኳን ለፍትህ ታጋይ መሆን፣ ገለልተኛ እንኳን ሆኖ ሳይታይ ከርሞ፣ ….ጭራሽ ከህዝብ በተመነተፈ ገንዘብ ጎኑን ሲያደላድል እንዳልኖረ፤ ዛሬ ቀን ሲለወጥ፣ ሚዛን ሲያጋድል መጥቶ፣ ደርሶ ለህዝብ ተቆርቋሪ፣ ደርሶ ኢትዮጵያን አፍቃሪ ሲመስል፤ ጭራሽ አፍ አውጥቶ ‹እኔም ለዚህ ለውጥ ስጮህ ነበር›› ሲል ሳይ እጅግ ስለከነከነኝ መናገርን ፈለግኩ፡፡ ‹‹መብቴ ነውና ህውሃትን ደግፌ ነበር›› ቢል አከብረው ነበር፡፡ ነገር ግን እኔም ለለውጥ ስጮህ ነበር ሲል ለእሱ ተሸማቀቅኩ፡፡
‹‹ስትጮህ አልሰማንህምሳ!›› አለችው ጠያቂዋ፡፡ …እውነቷን ነው፡፡ በህዝብ እህህ ማለት ዳንኪራ ከሚጨፍሩ ጋር አሸሼ ገዳሜ ሲል እንዳልኖረ፣ ህዝብ እሪ ሲል አብሮ እሰይ እንዳላለ፣ ህዝቡ ሲታረዝ እንዳልተሸቀረቀረ፣ ብዙሃኑ ሲራብ ጠግቦ ሲያገሳ እንዳልቆየ፣
በላባችን እንዳልወዛ፣
በድካማችን ደም ግባት እንዳላወጣ፣
በጉስቁልናችን እንዳልፋፋ ፣
ከአቆርቋዣችን ጋር በአንድ አልጋ እንዳልተኛ፣
‹‹እኔም ለዚህ ለውጥ ስጮህ ነበር‹‹ ሲል ምን ይባላል?
ተናግረው ያናግሩናል…..ማፈሪያ!