07/07/2024
Can Ethiopia be African medical tourism destination?
ኢትዮጵያ የአፍሪካ የሜዲካል ቱሪዝም መዳረሻ መሆን ትችላለች?
- በሰለሞን ማርቆስ (ፒ ኤች ዲ)
በጤናው ዘርፍ ጠንክረን ከሰራን ኢትዮጵያ የሜዲካል ቱሪዝም መዳረሻ (Medical tourism hub) መሆን ትችላለች።
ጥናቶች እንደሚያሳዩት የአፍሪካ ሜዲካል ኢንዱስትሪ በአመት እስከ 5 ቢሊየን ዶላር ሊያስገኝ የሚችል ትልቅ እምቅ የገበያ አቅም አለው። ይሁንና የአፍሪካ ሀገራት ዜጎች በሀገራቸው ጥራት ያለው ህክምና ስለማያገኙ ሌሎች ሀገራት ላይ ገንዘባቸውን ያፈሳሉ።
ኢትዮጵያዊያን በሀገራቸው መታከም ሲችሉ የተሻለ ህክምና ፍለጋ ወደ ህንድ፣ ቱርክ፣ ታይላንድ፣ ዱባይና ሌሎች ሀገራት እየሄዱ በአመት እስከ ግማሽ ቢሊየን ዶላር ያወጣሉ (አንዳንዶቹ ከህዝቡ ለምነው ያገኙትን ብር ሌላው ሀገር ላይ አስረክበው ይመለሳሉ።)
ከዚህም በላይ ሀገራችን በመቶ ሚሊየኖች የሚቆጠር ዶላር መድሐኒቶችንና የህክምና እቃዎችን ከውጪ ለማስመጣት ታወጣለች። አስቡት እንግዲህ የውጭ ምንዛሬ ከፍተኛ እጥረት ካለበት ሀገር ይህን ያህል የዉጭ ምንዛሬ በህክምና ምክንያት ከሀገር ሲወጣ።
የኢትዮጵያ መንግስት ለበርካታ ዘመናት መከላከልን መሰረት ያደረገ የጤና ፖሊሲ በመከተሉ ጥሩ ውጤት ያመጣ ቢሆንም በዛው ልክ ለከፍተኛ ህክምና ማለትም ለቴርሺያሪ ሆስፒታሎች የሰጠው ትኩረት በጣም አናሳ ነው።
ዛሬ ግን ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች እየተስፋፉ ከመምጣቸው ጋር ተያይዞ የከፍተኛ ደረጃ ህክምና አስፈላጊነት እየጨመረ መጥቷል። ነገር ግን የህዝቡን ጤና የሚጠብቁ በቂ ሆስፒታሎች የሉም። ያሉትም ቢሆኑ ከቀላሉ ከግሎቭ ጀምሮ ከፍተኛ የህክምና መሳሪያዎችና መድሐኒቶች እጥረት የሚሰቃዩ ናቸው።
ሆስፒታሎቻችን ዘመኑ የደረሰበት ቴክኖሎጂ በአብዛኛው ያልተሟሉላቸው፣ በከፍተኛ ደረጃ የሰለጠኑ ባለሙያዎች እጥረት ያለባቸው ናቸው። ከሁሉ የሚገርመው ኢትዮጵያ በከፍተኛ ደረጃ የህክምና ባለሙያዎችን እያስመረቀች ቢሆንም ለበርካታ ባለሙያዎች በቂ የስራ እድል ያልፈጠረች ነች።
እኛ ያልተጠቀምንባቸው ባለሙያዎቻችን ግን በሌሎች ሀገራት በከፍተኛ ደረጃ ተጠቃሽ የሆኑ ስራዎችን ሲሰሩ ይታያሉ። የባለሙያዎችን እውቀት ሳንጠቀምበት እየባከነ ይገኛል።
በቅርቡ ግን አዳዲስ መልካም ጅምሮች እያየን ነው። ኢትዮጵያ የሜዲካል ቱሪዝም መዳረሻ ለመሆን አቅዳ የአስር አመት ስትራቴጅክ ፖሊሲ አውጥታ መተግበር ጀምራለች። ትላልቅ ሆስፒታሎችን መገንባት ጀምራለች።
ለምሳሌም በቅርቡ በቢሾፍቱ የተመረቀው የመከላከያ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታልና ትላንት የተመረቀው የአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ ኮምፕርሄንሲቭና ስፔሻላይዝድ ሆስፒታሎች ተጠቃሽ ናቸው።
የመከላከያ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታልን በመረቁበት ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለባለስልጣኖቻቸው ከዚህ ቦኃላ ለህክምና ወደ ውጭ ሀገር መሄድ ሳያስፈልጋቸው እዚሁ አዲስ በተመረቀው ሆስፒታል እንድሚታከሙ ማሳስቢያ ሰጥተዋቸው ነበር። ይኼ እውነት ከሆነ ተስፋ ሰጪ ጅማሮ ነው።
በርግጥ ማንኛውም ሀገር በመንግስት አቅም ብቻ የሜዲካል ቱሪዝም መዳረሻ ለመሆን የቻለ የለም። ስለሆነም መንግስት የግሉ ሴክተር በተለይም አቅም ያለው የዲያስፖራ ኮሙኒቲ ገንዘቡን፣ ቴክኖሎጂና አቅሙን ይዞ መጥቶ ኢንቨስት እንዲያደርግ አበረታች ሁኔታዎችን ማመቻቸት አለበት። ሌላው በግልና በመንግስት ሽርክና ( public private partnership) ትላልቅ ሆስፒታሎችን መገንባት ይቻላል።
ስለዚህ ጠንከረን በእቅዱ መሰረት ከሰራን በአስር አመታት ውስጥ የአስር አመት ፖሊሲያችን እንደሚያስቀምጠው ከራሳችን ተርፈን ለሌሎች የውጭ ሀገር ህክምና ፈላጊዎች መዳረሻ መሆን እንጀምራለን።
የሜዲካል ቱሪዝም መዳረሻ መሆን ባንችል እንኳን ለህክምና የሚደረጉ የዉጭ ጉዞዎችን መቀነስ ከቻልን በሚሊየን የሚቆጠሩ ዶላሮችን ማዳን ይቻላል። ትልቅ ህልም ይዞ ጠንክሮ መስራት ወደ ምንፈልገው መዳረሻ ያደርሰናል።
Ethiopia Land of Origins Ethiopian Tourist Guides Professional Association የቱሪዝም ሚኒስቴር-ኢትዮጵያ Ministry of Tourism-Ethiopia ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር-ኢትዮጵያ Ministry of Culture & Sport-Ethiopia Ethiopian Holidays Ethiopian Wildlife Conservation Authority Great Ethiopian Run
Hakim