
19/06/2025
በዎላይታ ዞን ሶዶ ከተማ በ8 ዓመት ሴት ልጅ ላይ አስገድዶ በመድፈር የግድያ ወንጀል የፈጸሙ ተከሳሾች በዕድመ ልክ ጽኑ እስራት ተቀጡ
~~~~~~~~~~~
ዳዊት ሻንቆ እና ታምራት ኦሳ የተባሉ የሶዶ ከተማ ፋና ወምባ ቀበሌ ነዋሪዎች በቀን 16 /10/2016 ዓ.ም እሁድ ዕለት ከቀኑ 8:00 ሰዓት ላይ የሶዶ ከተማ ፋና ዎምባ ቀበሌ ነዋሪ የሆነችውን የስምንት ዓመት ህጻን መሳይ አስናቀን የግብረ ሥጋ ድፍረት በደል በመፈጸም ከፍተኛ ጉዳት ካደረሱባት በኋላ በገመድ አንጠልጥለው በመግደል ከባድ የሰው ግድያ ወንጀል መፈጸማቸውን የአቃቤ ህግ የምርመራ መዝገብ ያመለክታል።
በመሆኑም የክሱን ሂደት ሲመራ የነበረው አቃቤ ህግ በኢፌዴሪ የወንጀል ህግ አንቀጽ 32(1)(ሀ) እና 539 (1)(ሀ) የተደነገገውን በመተላለፍ የተፈጸመ ከባድ የሰው ግድያ ወንጀል ነው ሲል ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል።
በዚህም መነሻ በዛሬው ዕለት በቀን 12/10/2017 ዓ.ም በዋለው የወንጀል ችሎት የግራ ቀኝ አስተያየት በመመርመር ፍርድ ቤቱ አቃቤ ህግ ያቀረበውን ራሷን መከላከል በማትችል የስምንት ዓመት ህፃን ላይ የተፈጸመ ወንጀል ነው ሲል ያቀረበውን የቅጣት ማክበጃ አስተያየት በመቀበል ፍርድ ቤቱ ከተሰጠው የሥልጣን እርከን አንጻር ተከሳሾቹን ያርማል፣ ሌላውን ኅብረተሰብ ከመሰል ተግባር እንዲጠነቀቅ ማስተማሪያ እና ማስጠንቀቂያ ይሆናል ብሎ በማመን ተከሳሾች በዕድመ ልክ ጽኑ እስራት እንዲቀጡ በማለት በኢፌዴሪ የወንጀል ህግ አንቀጽ 32(1)(ሀ) እና 539 (1)(ሀ) እና በቅጣት አወሳሰን ቁጥር 2/2006 መሠረት ውሳኔ አስተላልፏል።
የሶዶ ከተማ አስተዳደር የሶዶ ከተማ ፖሊስ ታክቲክ ምርመራ ማስተባበሪያ ኃላፊ ኢንስፔክተር ታመነች ባሣ ወንጀሉ ተፈጽሞ ከተደበቀበት ከአራት ወር በኋላ ለከተማው ፖሊስ ጥቆማ በሟች እናት መደረሱን ገልጸው እንደገና የአካባቢውን ህዝብን በማስተባበር ምርመራ መደረጉን አውስተዋል።
ኢንስፔክተር ታመነች ባሣ አክለውም ቤተሰብ የልጆቻቸውን ውሎ በቅርበት እንዲከታተል እንዲሁም ለወንጀል ተጋላጭ ከሚያደርጉ ሁኔታዎች መጠበቅ እንዳለባቸው አሳስበዋል።
ህዝቡ የወንጀል ድርጊት ከማጋለጥ አንጻር የመረጃ ምንጭ በመሆን እያገለገለ እንዲሁም እየተባበረም እንደሆነ ገልጸው ምስጋናቸውን አቅርበው ከፖሊስ ጎን እንዲቆም ጠይቀዋል።
አለሚቱ ዳሮታ የሟች ልጅ እናት ስትሆን በመጨረሻ የተሰጠው ፍርድ ተገቢ እንደሆነ እና በልጄ ሞት ያዘንኩ ቢሆንም ፍትህ በመሰጠቱ ፍርድ ቤቱን የፍትህ አካላትን እና የሶዶ ከተማ ፖሊስን አመስግነዋል።
ሰኔ 12/2017
መረጃው የዎጌታ ኤፍ ኤም 96.6