19/03/2016
በአማራ ክልል የሆቴሎች ደረጃ ምደባ ይፋ ሆነ።
በክልሉ ለምዘና ከቀረቡ 58 ሆቴሎች 12ቱ የኮከብ ደረጃን እንዳገኙ ተገልጿል።
የኢፌዴሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ከአለም አቀፉ የቱሪዝም ድርጅት ጋር በመሆን በክልሉ በሚገኙ ሆቴሎች ላይ ሲያካሂዱት የነበረው ምዘና ውጤት ዛሬ ይፋ ተደርጓል።
በዚህም ለምዘናው ከቀረቡት ሆቴሎች መካከል ከቀረቡት መስፈርቶች አብዛኛውን ቢያሟሉም የእሳት አደጋ መከላከያ እና የጤና ማረጋገጫ ባለማቅረባቸው ደረጃ አልተሰጣቸውም።
19ኙ ደግሞ ከ30 በታች ውጤት በማስመዝገባቸው ከደረጃ በታች ናቸው ተብለዋል።
የእሳት አደጋ መከላከያ፣ ጤና ጉዳዮችንና በዘርፉ ብቁ የሰው ሀይል አሟልቶ መገኘት በሚኒስቴሩ ለሆቴሎች ምዘና ከተቀመጡት መስፈርቶች መካከል ናቸው።
በምዘናው ባሀርዳር የሚገኘው አቫንቴ ብሉናይል ሆቴል የአራት ኮከብ ደረጃን ያገኘው ብቸኛው ሆቴል ሆኗል።
እንዲሁም በባህርዳር የሚገኙት ቤማስ ሆቴል፣ አዲስ አምባ ሆቴል፣ ራሃን ሆቴል እና በጎንደር የሚገኙት ፍሎሪዳ ኢንተርናሽናል ሆቴል፣ ጃንተከል ሆቴል እና ጎንደር ላንድ ማርክ ሆቴል የባለ ሶስት ኮከብ ደረጃን አግኝተዋል።
የባህርዳር ፓፒረስ ሆቴልን ጨምሮ በጎንደር የሚገኙት ታየ በላይ ሆቴል፣ ኤጅ ሆቴል፣ ጉሃ ሆቴል እና ቋራ ሆቴሎች ደግሞ የባለ ሁለት ኮከብ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።
የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊ አቶ አወቀ እንየው ለሆቴሎች የሚደረገው ምዘናና ደረጃ የመስጠቱ ሂደት ቀጣይነት ይኖረዋል ብለዋል።
source: FBC