
19/07/2025
በችግር ውስጥ ኾኖም አበረታች የቱሪዝም ሥራዎች ተከናውነዋል።
=========+++======
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 12/2017 ዓ.ም የአማራ ክልል ምክር ቤት የሰው ሃብት አሥተዳደር እና ቱሪዝም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በሥሩ የሚቆጣጠራቸውን እና የሚደግፋቸውን ተቋማት የ2017 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም እየገመገመ ይገኛል።1
የባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ ኀላፊ መልካሙ ጸጋዬ የክልሉ ባሕል እና ቋንቋ አጠቃቀም እንዲያድግ እንደ ሻደይ፣ አሸንድዬ፣ ሶለል እና የመሳሰሉ ትውፊቶችን እና ክዋኔያቸውን በአግባቡ ማከናዎናቸውን በአብነት አንስተዋል።
የክልሉን ባሕል ለማሳደግ በጎንደር ከተማ "ድንቅ ባሕል፤ ድንቅ ምድር " በሚል ርዕስ ክልላዊ ፌስቲባል ተደርጓል ያሉት ቢሮ ኀላፊው በዚህም በክልሉ ከሚገኙ 22 ዞኖች ውስጥ 18ቱን አሳታፊ ማድረግ ተችሏል ነው ያሉት።
በዚህ ፌስቲባል ላይ የአፋር እና የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል የባሕል ቡድኖች እንዲሳተፉ በመጋበዝም ዘርፈ ብዙ ጥቅም ተገኝቷል ብለዋል ቢሮ ኀላፊው።
የአማራ ክልል የበለጸገ የባሕል ባለቤት ቢኾንም የተጠናከረ የሽምግልና ማኀበር አልነበረውም ያሉት አቶ መልካሙ ለሰላም እና ለባሕል እሴት ግንባታ በክልሉ ካሉት 22 ዞኖች የተመረጡ ሽማግሌዎችን በማኀበር ለማቀፍ ተሠርቷል ነው ያሉት።
በክልሉ ውስጥ በባሕል ኢንዱስትሪው ውስጥ ለተሰማሩ የዕደ ጥበብ ባለሙያዎች የገበያ ትስስር በመፈጠሩ ምርታቸውን ለውጭ ሀገር እንዲያቀርቡ አስቻይ ኹኔታዎች መመቻቸታቸውን ቢሮ ኀላፊው ተናግረዋል።
ቢሮው የሀገር በቀል ዕውቀትን ለማስፋፋት ተግቶ እየሠራ ነው ያሉት አቶ መልካሙ የብራና ሥራ ሥልጠና ተሰጥቷል። አንባቢ ትውልድን ለመፍጠርም በክልሉ በበርካታ አካባቢዎች ቤተ መጻሕፍቶች እየተስፋፉ ነው፤ በግብዓት እየተሟሉም ይገኛሉ ነው ያሉት።
የቱሪዝም መሠረተ ልማት አቅርቦትን በማስፋፋት የኀብረተሰብ ተሳትፎን ማሳደግ ስለመቻሉም አስረድተዋል።
የዘጌ ባሕረ ገብ መንገድን በመሥራት ለቱሪስቶች ምቹ የማድረግ ሥራ መከናወኑንም አውስተዋል።
እንደ ሀገር በተገነባው አንድነት ፖርክ ውስጥ የአማራ ክልልን ሕዝብ በወጉ እና የሥራውን ያህል ወካይ የኾነ የለውም የሚለውን ቅሬታ በመገንዘብ እና ትኩረት በመስጠት ወካይ ዲዛይን ተዘጋጅቶ ወደ ሥራ ተገብቷል ብለዋል።
የክልሉን የመስህብ ሃብት ለማስተዋወቅ መደበኛ የመገናኛ ብዙኅንን እና ማኀበራዊ ሚዲያዎችን በመጠቀም ሰፊ ሥራ ተሠርቷል፤ በዚህም አበረታች ውጤት ተገኝቶበታል ነው ያሉት።
ከ5 ሚሊዮን በላይ የሀገር ውስጥ እና ከ27 ሺህ በላይ የውጭ ሀገር ቱሪስቶች ክልሉን የጎበኙት በተከናወነው የማስተዋወቅ ሥራ መኾኑን አንስተዋል።
ቢሮ ኀላፊው በክልሉ ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ጋርም ትብብር ዐውደ ጥናት በማቅረብ ጥሩ ግብዓት ተገኝቷልም ብለዋል።
ዘገባው: የአሚኮ ነው።
"ድንቅ ምድር- አማራ"ን ይጎብኙ!
Amhara Culture & Tourism Bureau
# Visit Amhara
ወቅታዊና ትኩስ መረጃዎች እንዲደርሳችሁ የፌስቡክ ገጻችንን ይወዳጁ ያድርጉ 👇👇👇👇👇
https://www.facebook.com/profile.php?id=100057096864608&mibextid=ZbWKwL