08/11/2023
በቀጠለዉ ዉግያ በላሊበላ የድንጋይ ውቅር አብያተ ክርስቲያን ላይ አደጋ ተጋርጧል
በላሊበላ አካባቢ ስላለዉ ነገር ይጻፉልን!
አማራ ክልል ውስጥ በመንግሥት የጦር ኃይል እና በአካባቢው ታጣቂዎች መካከል የቀጠለው ውግያ ታሪካዊ ቅርሶችን ለጉዳት ያጋልጣል የሚል ስጋት መኖሩ ተዘገበ።
ባለፈዉ እሑድ የመንግሥት ወታደሮች በላሊበላ የድንጋይ ውቅር አብያተ ክርስቲያን አቅራቢያ 11 ጊዜ ከባድ መሣሪያ መተኮሳቸው ጉዳት ሊያመጣ የሚችል ንዝረት ማስከተሉን የአካባቢው እማኞችን ጠቅሶ ሮይተርስ ዛሬ ዘግቧል። አካባቢዉ ላይ አዲስ ዉግያ መቀጠሉን ሮይተርስ ያነጋገራቸዉ ሁለት የዓይን እማኞች አረጋግጠዋል። ከላሊበላ ወጣ ብለው እና በአውሮፕላን ማረፊያው አካባቢ የሰፈሩት የመንግሥት ወታደሮች ቅዳሜ ዕለት ውግያውን መጀመራቸውን፤ ከባድ መሣሪያዎችን ወደ ተራራው መተኮሳቸውን ገልጸዋል። በአሁኑ ጊዜ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የሚገኙት በላሊበላ አካባቢ ማደጋቸው የተገለጸው ፖለቲከኛ ልደቱ አያሌው በበኩላቸው በተጠቀሰው ስፍራ ከባድ የጦር መሣሪያ መተኮስ ታሪካዊ ቤተ ክርስቲያኖቹን ለጉዳት ሊያጋልጥ እንደሚችል መግለጻቸውን ዘገባው ጠቅሷል። በጉዳዩ ላይ የመንግሥት ቃል አቀባዮችም ሆኑ የአማራ ክልል መስተዳድር እንዲሁም ከመከላከያ አስተያየት ማግኘት እንዳልቻለም ሮይተርስ ዘግቧል። በላሊበላ አካባቢ ስላለዉ ነገር ይጻፉልን!